የአእምሮ ጤና ግንዛቤ ለSOGIE ማህበረሰብ

ጤና ምንድን ነው?

የአለም ጤና ድርጅት“ጤና የተሟላ የአካል፣ የአእምሮ እና የማህበራዊ ደህንነት ሁኔታ እንጂ የበሽታ ወይም የአካል ጉዳት አለመኖር አይደለም”ሲል ገልጾታል።

የአእምሮ ጤና ምንድነው?

የአዕምሮ ጤና ሰዎች የህይወት ውጣ ውረዶችን እንዲቋቋሙ፣ ችሎታቸውን እንዲገነዘቡ፣ በደንብ እንዲማሩና እንዲሰሩ እንዲሁም ለህብረተሰባቸው አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ የሚያስችል የአእምሮ ደህንነት ሁኔታ ነው። የአዕምሮ ጤና የግል እና የጋራ ችሎታችንን በመጠቀም ውሳኔ እንድናደርግ፣ ግንኙነቶችን እንድንገነባ እና የምንኖርበትን ዓለም እንድንቀርጽ የሚረዳን የጤናችን እና የደህንነታችን ዋና አካል ነው።

የአእምሮ ጤና ለግል፣ ለማህበረሰብ እና ለማህበረ-ኢኮኖሚያዊ እድገት ወሳኝ የሆነ መሰረታዊ የሰው ልጅ መብት ነው። የአእምሮ ጤና ከአዕምሮ ጤና መታወክ አለመኖር የበለጠ ነገር ነው። አንድ ሰው የሚያጋጥመው የአዕምሮ ጤና ይዘት ውስብስብ በሆነ መልኩ ከሌላ ሰው ልምድ የተለየ በመሆኑ ከሰው ሰው ላይ የሚያሳድረው ችግር እና የጭንቀት ደረጃ የተለያየ የማህበራዊ እና የህክምና (clinical) እንደምታዎች ላይ እንድንደርስ ሊያደርገን ይችላል።

የአእምሮ ጤና እክል (disorder) ምንድን ነው?

የአዕምሮ ጤና እክል ምልክት የግለሰቦች የአእምሮ ተግባርና ክንውን ጊዜ በጉልህ በሚታይ ችግር፤ ሰሜትን ባለመግዛትና ከተለምዶው የተለየ የአዕምሮ እክልን በሚያሳይ ባህሪ ሲረበሽ እንዲሁም በህክምና የተረጋገጠ የስነ-ልቦና ፣ ስነ-ሕይወታዊ ወይም የአዕምሮ እድገት ሂደት እንቅፋት ሲኖር የሚስተዋል እና የሚገለጽ የጤና እክል ምልክት ነው። የአእምሮ ጤና እክል ብዙውን ጊዜ በማህበራዊ ህይወት፣ በስራ ገበታ ወይም በሌሎች አስፈላጊ የህይወት ተግባራት ውስጥ የሚኖር ሚናን መወጣት ካለመቻል እና ከከፍተኛ ጭንቀት ጋር የተቆራኘ ነገር ነው።

የአእምሮ ጤና መዛባት መንስኤው ምንድን ነው?

የአእምሮ ጤና መዛባት የሚያስከትሉ በርካታ ምክንያቶች አሉ። እነሱም በሶስት ተከፍለዋል።

  1. የዘረ መል (Genetic) መንስኤ: (በተዋልዶ ከወላጆች በቀጥታ በዘረ መል የሚወረሱ ባህሪያት)
  2. አካባቢያዊ መንስኤ (በልጅነት የሚደርስ አስፈሪ አደጋና ሰቀቀን፣ ጥቃት፣ ሁከት፣ ጦርነት፣ የጉልበተኞች ጥቃት፣ የመሳሰሉት)
  3. የአንጎል ጉዳት፡ (አሰቃቂ የአንጎል ጉዳት, በኢንፌክሽን ወይም በመድሃኒት አጠቃቀም ምክንያት የሚመጣ የነርቭ ኬሚካል አለመመጣጠን፣ የመሳሰሉት)

በSOGIE ማህበረሰብ ውስጥ የአእምሮ ጤና እክል ምን ያህል ተስፋፍቷል?

ከአጠቃላይ ማህበረሰቡ ጋር ሲነፃፀር የSOGIE ማህበረሰብ በበለጠ የአዕምሮ ጤና እክል ይሠቃያል። ይህም በዋነኝነት ምክንያቱ ከማህበረሰቡ የሚደርስብን የቡድን ጥቃት (ማግለል እና መድልዎ) ከቤተሰብ ፣ ከጓደኞች ፣ ከሕዝብ እና ከሌሎች የማህበረሰቡ አባላት አልፎ ተርፎም ከራሳችን ማህበረሰብ ጭምር ስለሚሰነዘር ነው። ይህም ጥቃት ራሳችንን መቀበል እንዳንችል ቀጥሎም ለከፍተኛ ጭንቀት እንድንጋለጥ አድርጎናል።

የ SOGIE አካል መሆን በራሱ የአእምሮ ጤና እክል ስለሆነ አይደለም። እንደ SOGIE ያሉ የተገለሉ ሰዎች የጤና ጥበቃ ማዕከላት፣ የሃይማኖት ተቋማትና በህግ በመሳሰሉት ዓይነት ተቋማት ውስጥ ዕድልን፣ ሀብትን (Resource) እና ሁለገብ ደህንነትን በፍትሃዊነት እንዳይጠቀሙ ስለተገደቡ ለጭፍን ጥላቻ እና መገለል ተጋልጠዋል።

እ.ኤ.አ. በ 1973 የአሜሪካ የስነ-ልቦና ማህበር የተመሳሳይ ጾታ ተማርኮን እንደ የአእምሮ ህመም ይቆጥር ነበር ። ይህ ውሳኔ የተደረገ የአንጎል ፓቶሎጂ ሳይንቲስቶች ባጠኑት ጥናት ላይ በመመርኮዝ ሳይሆን ይልቁንም በጊዜው የነበረው ማህበረሰብ እምነት ምክንያት ነበር፤ በኋላ ግን ከመመርመሪያ እና ከስታቲስቲካዊ የአእምሮ ጤና እክሎች መደብ (DSM) እንዲወጣ ተደርጓል።

ጠቃሚ ምክሮች

  • የአእምሮ ጤና እክል በክፉ መንፈስ በመያዝ የሚከሰት አይደለም።
  • የ SOGIE አካል መሆን የአእምሮ ጤና መታወክ አይደለም።
  • የአእምሮ ጤና ልክ እንደ አካላዊ ጤንነት ወሳኝ ነው።
  • የአእምሮ ጤና እክል ሊታከም /መፍትሄ ሊያገኝ ይችላል.

በSOGIE ማህበረሰቦችሰባችን ውስጥ በጣም የተለመዱትን የአእምሮ ጤና መታወክ ዓይነቶች የሚያጎላውን ቀጣዩ ጽሑፋችንን ይጠብቁ።

ዶ/ር ዜማ

Share