ማን ነን

እኛ የLGBTQ+ ግለሰቦችን ከፍ ለማድረግ ቆርጠን የተነሳን የLGBTQ+ አክቲቪስቶች ነን። ተልእኳችን በእውነተኛነት የመኖር፣ ፍቅራችንን የመግለጽ፣  መከባበርን እና እኩልነትን በሚያበረታታ ማህበረሰብ ውስጥ ትርጉም ያለውና የተሟላ ህይወት እንድንኖር እና መሰረታዊ መብቶቻችንን ከአድልዎ፣ ከጭቆናና እስራት በጸዳ መልኩ ማስከበር ነው። የፆታ ዝንባሌያችን ወይም የፆታ ማንነታችን ምንም ይሁን ምን በጋራና በተናጥል በምናበረክተው አስተዋጽዖ እያደግን የበለጠ አካታች እና ተቀባይነት ያለው ማህበረሰብን ለመፍጠር እንተጋለን።

ለምን ተመሰረትን

ፋዪዳ-ኢትዮጵያ የተመሰረተው ግልጽ ተልዕኮ የLGBTQ+ ማህበረሰብ መብቶች ላይ የሚቃወሙ አድሎአዊ ህጎች እንዲወገዱ እና በሁሉም አይነት አድሎዎች ላይ በንቃት ዘመቻ ለማድረግ ነው። ማግለልና መድልዎ ሥር የሰደደው ማህበረሰቡ በፈጠረው ጎጂ ባህል፣ ማህበራዊ ደንብ እና በሃይማኖት ስም በሚተላለፉ ጎጂ ግንዛቤዎች እንደሆነ እንገነዘባለን። ድርጅታችን የፆታ ተማርኮ ዝንባሌያቸው ወይም የስርዓተ ፆታ ማንነታቸው ምንም ይሁን ምን እነዚህን ጎጂ ባህሎችና ትረካዎችን ለማክቸፍ እና አብሮ ለመቅረጽ፣ ለሁሉም ሰው የሆነ ሁሉን አሳታፊ እና አክባሪ ማህበረሰብን ለማፍራት ቁርጠኛ በመሆን የተቋቋመ ነው።

እኛ የምንሰራው

ፋዪዳ-ኢትዮጵያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፐሮግራሞችን በመቅረጽ የ LGBTQ+ ግለሰቦችን መብት እና እኩልነት ለማስጠበቅና በእኛ ላይ የሚደርሱ ኢ-ፍትሃዊ ማህበራዊ ድርጊቶችን ለመታገል በለውጥ ግንባር ለመሄድ ተነስታለች። ድህረገጾችን በመጠቀም በምንሰራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በኢትዮጵያ ውስጥ በጾታ ተማርኮ ዝንባሌያቸው፣ በስርዓተ-ፆታ ማንነታቸውና ራሳቸውን በመግለጻቸው የተገለሉ ማህበረሰቦች ላይ ኢ-ፍትሃዊ በሆነ ሁኔታ ተጽዕኖ የፈጠሩ አሉታዊ ማህበራዊ ደንቦችን እንዲፈትኑ እና እንዲጠይቁ በማድረግ ሃሳብዎን ለበጎ እንዲቀሩ የራሳችንን አስተዋጽዖ እናበረክታለን። አላማችን መሰናክሎችን በማፍረስ የኛን ማህበረሰብ ያሳተፈ፣ ፍትሃዊና በብዝሃነት ተቀባይነት ያለው ለሁሉም እኩልነትን የሚያጎናፅፍ መጪ ጊዜን መፍጠር ነው።

እኛ የፋይዳ ቡድን ሃገሪቱ ውስጥ ያሉ ባህሎች፣ ሀይማኖቶች እና ወጎችን እናከብራለን። ቅርሶቻችንን ከሰብአዊ መብታችን እና ከማንነታችን ጋር በማይጋጭ መልኩ ማካተት እንደምንችል እናምናለን። አለም ሁሌም የምትለዋወጥ ናት። የተሻለ ህይወት ለመፍጠር ባህሎች እና ወጎች እንደሚለዋወጡ እናምናለን። ወግ አጥባቂ ሃይማኖታዊ እሴቶች በተሻለ አቅጣጫ በማየት ለበጎ ሊለወጡ ይችላሉ።

በLGBTQ+ ማህበረሰብ ውስጥ እውነተኛ ተሞክሮዎችን በማካፈል፣ መግባባትን ለማጎልበት፣ ክፍተቶችን በመቅረፍ እና የበለጠ አካታች እና ተቀባይነት ያለው ማህበረሰብ ለመፍጠር የእኛ መድረክ የለውጥ አጋዥ ሆኖ ያገለግላል። በአለም ዙሪያ ያሉ የኩዌር ሰዎች እውነተኛ የህይወት ታሪኮች እና ልምዶች እራስዎን በእነርሱ ጫማ ውስጥ አስገብተው እያዩ እራስዎን ይበልጥ ለማወቅ እና በህይወት ውስጥ ለመጓዝ ይረዳኛል ብለው እንደሚያስቡ ተስፋ እናደርጋለን።