ክርስትና እና እኔ

እንደመግቢያ 

በእዚህ ፁሁፍ ማንሳት የፈለኩት ሀሳብ መነሻው ባለፉት ስምንት ወራት በኢትዮጵያ በተለይም በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እኔን እና እኔን መሰል የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ላይ የተነሱ የግድያ ዛቻዎች፣ ከባድ አካላዊ ጥቃቶች ፣ ፀያፍ ስድቦች እና ሌሎችም ነገሮችን በማየቴ ነው። ለአብዛኛው እና ወረት ለሚመስለው የማህበራዊ ጅምላ ጥላቻ መሠረታዊ ምክንያቱ ሐይማኖታዊ አስተምህሮዎች ይመስሉኛል ። ለእዚህም በተለይ በክርስትና እምነት ላሉ ቀጥ ወዳጆቼ ወዳጃዊ ጥያቄ ማቅረብን መረጥሁ። እነዚህ ጥያቄዎች ምንም አይነት ሀይማኖታዊ ዶግማንና ቀኖናን የሚነኩ ሳይሆኑ አንድ ክርስትናውን እና ተፈጥሯዊ ማንነቱን ለማስታረቅ ላለፉት 8 ዓመታት የለፋ ሰው ጥያቄዎች ናቸው። እኔና መሰሎቼ ከወል ድባቴ እና ትሮማ ለማምለጥ የምናደርገው መፍጨርጨር ከእነዚህ ከማነሳቸው ሀሳቦ ይያያዛሉ ብዬ አስባለሁ። መኖር ቀቢጸ ተስፋ ፣ ወጦ ሰርቶ መግባት የዕለት ከዕለት ችግር ለሆነብን ለእኛ በሰዋዊ ፍቅር ጥያቄዎቻችንን የሚሰማን ማግኘት ትልቅ ነገር መሆኑን አምናለሁ።

፩. ክርስትና እና ቅዱሳን መፅሐፍት 

በክርስትና ቅዱሳን መጻሕፍት በተለይም  መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያናዊ ህይወትን፣ ዶግማን፣ እምነትን እና ቀኖናን የመበየን ተፈጥሯዊ ስልጣን አላቸው። በተለያዩ ዘመናት የተነሱ የስነመለኮት እና የትርጓሜ መምህራን መጽሐፍ ቅዱስን ሲተረጉሙ እና ህግና ስርዓትን ሲያበጁበት ቆይተዋል። 

በእዚህም በተለያዩ ዘመናት የመጡ መምህራን ክርስትናቸውን የሰው ልጅ ከደረሰበት የእውቀት፣ የስልጣኔ እንዲሁም ከዘመኑ ጥያቄዎች ጋር እያስታረቁ እዚህ ደርሰዋል። ለእዚም የቅዱሳን መጽሐፍት ትርጓሜ በተለያዩ ጊዜያት ሲስተካከሉ እና ሲቃኙ ተስተውለዋል።

1. ከመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች አንዳንዶቹ የብሉይ ኪዳንን የመገረዝ ኪዳን እና ህግን ያልፈፀመ ሁሉ ወደአዲሱ እና በክርስቶስ ከሚገኘው ልጅነት ተካፋይ ሊሆን አይገባም እያሉ ያስተምሩ ነበር። የቀደመ ለአብርሃም የተሰጠውን ህግ መሰረት አድርገው ማስተማራቸው ትክክል ቢሆንም ጴጥሮስ ግን የመገረዝን ህግ ውድቅ አድርጎ በክርስቶስ የሚገኘው ልጅነት ኢየሱስን በማመን ብቻ የሚገኝ መሆኑን ሲያስተምር እናያለን። (የሐዋርያት ስራ 15፣8-10)

2. ከዛሬ መቶ እና መቶ አምሳ ዓመት በፊት የሰው ልጅ ሌላውን የሰው ልጅ እንደእንስሳ ገዝቶ በባርነት ይገዛ ነበር። በእዚህም ክርስትያኖች እንደግለሰብ እንዲሁም እንደተቋም የሮም ካቶሊክ ቤተክርስቲያን እና ሌሎችም አብያተክርስቲያናት በባርነት ንግድ ተሳትፈዋል። ይህ እንዲሁ የመጣ ሳይሆን ለ1800 ዓመታት ክርስትና ቅዱሳት መጽሐፍትን እየጠቀሰ ባርያን ማሳደር ኢሞራላዊ ድርጊት እንዳልሆነ ስላስተማረ ነበር። ነገር ግን በ19ኛው መቶ ክፍለዘመን ክርስቲያኖች ባርነትን የሚደግፉ የቅዱሳን መጽሐፍትን የረዥም ጊዜ ትርጓሜ ደግመው እንዲያጤኑት በዘመኑ ከነበሩ የባርነት ስርዓት ከሚቃወሙ ብዙ ሰዎች ይጠየቁ ነበር። በእዚህም በተለይ እንደዊሊያም ዊልበርፎርስ ያሉ እና ሌሎች የክርስትናው ዓለም ሰዎች ክርስቲያኖች የባርነት አስከፊ እውነታን እንዲያውቁ በማድረግ እና ለማህበረሰባዊ ለውጥ እና እድገት በመስራት የባርነት ስርዓትን ታግለዋል። 

በእዚህም በቅርቡ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን፣ የአንግሊካን ቤተክርስቲያን እና የመጥምቃዊያ አብያተክርስቲያናት በይፋ የነበራቸው አቋም እና አረዳድ ስህተት መሆኑን አምነው ይቅርታ ጠይቀዋል።

3. “ማስተዋልን፣ ማመዛዘንን እና ምክንያታዊ እውቀትን የሰጠን ያው አምላክ እነርሱን ከመጠቀም እንድንርቅ የሚፈልግ አይመስለኝም።” ይህን ንግግር የተናገረው በዘመናዊ ሳይንስ ታሪክ ውስጥ ስሙ በጉልህ የሚነሳው ጋሊልዮ ጋሊሊ ነው። በቤተክርስቲያን የመጀመሪያዎቹ 1600 ዓመታት ውስጥ ሁሉም ክርስቲያኖች ማለት ይቻላል ምድር በጽንፈ ዓለሙ (universe) መካከል እንደቆመች ያምኑ ነበር። (መዝ 93፣ ኢያሱ 10፣ መክ 1) ነገር ግን የቴሌስኮፕ ፈጠራ ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስን አተረጓጎም እንደገና እንዲያጤኑት አድርጓቸዋል።

ከላይ ያነሳኋቸው በአብዛኛው የክርስትናው ዓለም ያሉ ትርጓሜያቸው እንደገና የተጤኑ ሀሳቦች ይሁኑ እንጂ በተለያዩ የክርስትና ቤተ እምነቶች የቅዱሳን መጽሐፍት ትርጓሜ በተለያየ ጊዜያት ተከልሷል።

በእኔ እምነት ክርስትና ዛሬም ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የወደቀ ይመስለኛል። ዛሬ ስለፆታዊ ዝንባሌዎች ባገኘናቸው አዳዲስ መረጃዎች ምክንያት ባርነት ፣ ግርዛት እና ሌሎችም ላይ ያሉ አስተምህሮዎች እንደተጤኑ ሁሉ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ላይ ያለው ኢሞራላዊ አስተምህሮም መቀየር አለበት።

በጥንቱ ዓለም የተመሳሳይ ፆታ መስህብ እንደሃጥያት እና ብልግና ይታይ እንጂ በጥንታዊ የግሪክና የሮም ሰዎች ዘንድ መደባዊ ስርዓቱን ከጠበቀ ተቀባይነት ነበረው። ለምሳሌ አንድ ሮማዊ ዜጋ በባርነት ከሚያሳድረው ወንድ ጋር ወሲባዊ ተራክቦ ቢያድርግ ጥብቅ የሆነውን መደባዊ ስርዓት ውስጥ የበላይነቱን እንደማሳያ ይቆጠር ነበር። በእዛ ዘመን ፆታዊ ማንነት የሚገለፀው በፆታዊ ዝንባሌ ሳይሆን አባታዊ በሆነው የስርዓተ ፆታ ሚናዎች ጋር በመስማማቱ ብቻ ነበር። በወሲባዊ ተራክቦ ላይ የበላይ የነበሩ ወንዶች ከወንዶች፣ ከሴቶች ወይም ከሁለቱም ጋር ወሲባዊ ተራክቦ ቢያደርጉ በአውንታዊ መልኩ ይታይ ነበር። ስለዚህም የግሪኮ-ሮማን ማህበረሰቦች ውስጥ አባታዊ ስርዓቱን የተጠበቀ ፆታዊ መስህብ ተቀባይነት ነበረው። አንዳንድ ጥንታዊ ጹሁፎችም ተፈጥሮአዊ ፍቅር መሆኑን ተናግረዋል። ከፕልቶ ሲፖዚየም (አሪስቶፋነስ የተባለው ገፀባህርይ )እስከ ኔሮ ከባርያው ጋ እሰካደረገው ጋብቻ ድረስ ምሳሌዎች አሉ።

፪. የእኔ ጥያቄዎች

1 ፆታዊ መስህብ ምርጫ ወይስ ተፈጥሮ? ከክርስትና መሰረታዊ አስተምህሮዎች የሰው ልጅ ሁሉ ምርጫ አለው እሱንም የመምረጥ ነፃነት (ነፃ ፍቃድ) አብሮ አለው የሚለው አንዱ ነው። ከእዚህ በመነሳት ብዙ ክርስቲያን ወዳጆቼ ለተመሳሳይ ፆታ ያለህ መስህብ የአንተ ምርጫ እንጂ ተፈጥሮህ አይደለም ይሉኛል። የመረጡሁት ማንነት ቢሆን በጣም ደስ ይለኝ ነበር። ለመሆኑ የቱ ሰው ነው መገፋትን፣መገደልን እና እንደአውሬ መታየትን የሚመርጠው? ነገር ግን ለተቃራኒ ፆታ አፍቃሪ ወዳጆቼ የማነሳው አንድ ቀላል ጥያቄ ነው ” እናንተ የተቃራኒ ፆታ መስህብ ያላችሁ ሰዎች ዛሬ ተነስታችሁ ለተመሳሳይ ፆታ መስህብ እንዲኖራችሁ ትመርጣላችሁ?” አንዱ ወዳጄ “ማሰብ ራሱ አልችልም።” አለኝ። ትክክል ነው ከተፈጥሮው ውጭ እንዴት ያስባል?. 

  
2. የተለያዩ ክርስቲያኖች የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪነት ተፈጥሮአዊ አይደለም ይላሉ። ስለዚህም ይህ ፍቅር ኢሞራላዊ ተግባር ነው ይላሉ። ነገር ግን ተፈጥሯዊ አይደለም ሲባል ምን ማለት ነው?  ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዓለም ላይ ከሁለት ቢሊዬን በላይ ሰዎች በተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪነት ጥላ ውስጥ ይካተታሉ። እነዚህ ሁሉ የእግዚአብሔር ፍጡራን ተፈጥሯቸው የተዛባ ነው እያላችሁ ነው?

በእድሜዬ ነገሮችን ማወቅ እና ማስታወስ ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ ተቃራኒ ለሆነ ፆታ ምንም አይነት መስህብ የለኝም። ከሰፈሬ አቧራ ሜዳ እስከ ትምህርት ቤቴ ለወንዶች ፆታዊ መስህብ እና ፍቅር አለኝ። እና ይህ የእኔ ተፈጥሮ አውሬአዊ ነው? ይልቁንም የተነገረኝ ተፈጥሮዬ በሳይጣናዊ መንፈስ እንደተያዘ ነበር። ራሴን ለመፈወስ ከወንቅሸት ገብርኤል እስከ ብዙ የእምነት ቦታዎች ተመላልሻለሁ። እንዴት ዓለም ላይ ያለን ሁለት ቢሊዮን ሰዎች ሳይጣናዊ ማንነት ይኖረናል?

በመጽሐፍ ቅዱስ ከተፃፉ ታሪኮች መካከል የሳምራዊቷ ሴት አንዱ ነው። በእዛ ዘመን ሳምራዊ መሆን ማለት ከተፈጥሮ መጉደል ከሰውነት ማነስ ነበር። አይሁድ አይደለም አብረዋቸው ሊጠጡ እቃ ሊዋሷቸው፣ በሰፈራቸው ሊያልፉና ሰላም ሊሏቸው የማይፈልጓቸው ነበሩ። ነገር ግን ኢየሱስ ከሳምራዊቷ ሴት ውሃን ለመነ ደሞም የእሷን እና የመሰሎቿን  እንደሰው የመቆጠር ሰዋዊ ክብር የማግኘትን ጥም ቆረጠላቸው። እግዚአብሔርዊ ተፈጥሮአቸው ሳይሆን የደቦ ማህበረሰባዊ እሳቤ በዳያቸው ነበር። እኛስ? የዘመኑ ሳምራውያን እንሆን? ከተፈጥሮ ማህበረሰብ ያጎደለን ውብ ፍጥረቶች!

3. ሌላኛው መከራከሪያ የወሲብ ግቡ አምሳያን መተካት ነው ስለዚህም የተመሳሳይ ፆታ ወሲብ ግብ የለሽ ነው የሚለው ነው። ወሲብ ሁሉ ለመውለድ የሚደረግ ተግባር ነው የሚለው ሀሳብ ባዮሎጂ እና ስነተዋልዶ ካለማወቅ የመጣ ይመስለኛል። ሁላችንም እንደምናውቀው ወሲባዊ ተግባቦት የፈፀሙ ሁሉ አይወልዱም። ስለዚህ ወሲብ ግቡ ልጅ መውለድ ነው ከተባለ በተፈጥሮ ልጅ መውለድ የማይችሉ ሰዎችም ወሲባዊ ተግባቦት አይኑራቸው ማለት ነው? ከእዚሁ ጋር በተያያዘ የሚነሳው በተለይ የፊንጢጣ ወሲብን እንደ ኢተፈጥሮአዊ ነገር ማየት ነው። በመጀመሪያ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪነት ወሲባዊ መስህብ ብቻ አይደለም አፍቃሪነትና የፍቅር ህይወት ነው። ሌላው የፊንጢጣ ወሲብ ከተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን በበለጠ በተቃራኒ ፆታ አፍቃሪያንም ዘንድ በስፋት ይዞተራል።

እንደማጠቃለያ

ክርስትና በክርስቶሳዊ ፍቅር የተገመደ ሀይማኖት ነው። ለአዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ሁለት መሰረታዊ ህጎች የተሰጡ ይመስለኛል። አንዱ እግዚአብሔር የሰውልጅ ሁሉ ስለመተላለፉና ስለሀጢያቱ መዳን የሰጠውን አንድያ ልጁን ማመን ነው። (1ኛ ዩሐንስ 3፣23 ) ሌላው ደግሞ የሰውን ልጅ ሁሉ በክርስቶሳዊ ፍቅር መውደድን ነው። ነገር ግን ዛሬ ክርስቲያኖች ለመግደል ለመደብደብ እና ለመሳደብ ቅርብ ናቸው። 

   “ስንት አለ

   ለኢየሱስ ሲሞገት ፣ ስሙ የገነነ

   ምስክር ተብሎ፣ ጠበቃ የሆነ!”

እንዳለው ባለቅኔው ብዙ ክርስቲያኖች ከክርስቶሳዊ ፍቅር በበለጠ አሳዳጅነትን ይመርጣሉ። ነገር ግን ለእኔ እና ለመሰል የተመሳሳይ ፆታ አፍቃርያን ህይወት ታላቅ በረከት አይደለም። ህልማችንን ለእዚህ ዓለም ማድረግ የምንችለውን በጎ ነገር ሁሉ በተለጠፈብን ማህበራዊ እና ሐይማኖታዊ ማንነቶች ወደኋላ ቀርተናል። ለእኛ ህይወት ውጣውረዱ የሚያድክም፣ገብቶ መውጣቱ የሚያደክም እና ቀበሩ የሚያጎብጥ ነው። ለምን?

HenaAb 2016

Share