ለጓደኛዬ ነገርኩት

አንዳንድ ለሊቶች አሉ አይደል በመገላበጥ የምንጨርሳቸው? ለምን? እንዴት? በሚሉ መልስ በሌላቸው ጥያቄዎች የሚረዝሙ ለሊቶች.. አይቀርም ደሞ ይነጋል። ወደ ምንጠላው ጠዋት እንነቃለን። ለምን ያልነውን ሳንጨርስ እኮ እንዴት? እንላለን። እንነግረው ወዳጅ እናዋየው ሰው እንፍልጋለን።

 አለ፦

የሚያጋሩት እዳ

የሚወጡት ፍዳ

የሚነግሩት ወሬ

የሚታከሙት ደዌ

አለ፦

ህማም -የመረረ፥

ስቃይ -የተሰወረ፥

የማይነግሩት -ለሰው፥

የማይችሉት -ይዘው።

እንዳለው ገጣሚው ፍዳችንን የምንዘረግፍለት፣የመዳኒቱን ብልቃጥ የሚነግረን ሰው እንፈልጋለን። ግን ማን?  እንዴት ተብሎስ ይነገራል? ምንስ ተብሎ ይጀመራል?

ይህ የእኔ እውነት ነበር። ከራሴ ጋር በመጣላት ራሴን መቅጣት ሱስ ያደረኩ ሰው ነበርኩ። ሌሊቶቼን በእንባ፣ ቀኖቼን በቁጭት የማሳልፍ፣ የጎደልኩ  የታመምኩ ያክል የሚሰማኝ፣እነግረው ሰው ያጣሁ ፣ ማንነቴን ህመሜ አድርጌ የቆጠርኩ ሰው ነበርኩ። አንዳንዴ ማሰብን እንዴት አለማሰብ እንደምችል ሳስብ ይነጋል። በጣም ሲበዛብኝ  ወደምደበቅበት ዋሻዬ እሄዳለሁ። አምልጠው ይመስል ራሴን ራሴ ጠልቸ ሂድልኝ እለዋለሁ። ሁላችንም መደበቂያ አለን አይደል? የማናመልጥበት ግን የምንረሳበት ዋሻ? እኔም ዘው ብዬ እገባለሁ። 

ዛሬም ራሴን ከሃሳብ ጅረት ለማስመለጥ ከምወደው ጓደኛዬ ጋ ረጅም ወክ ወጣሁ። “ደህና ነህ?” አለኝ። ለእዚህ ጥያቄ ብዙ ጊዜ የምመልሰው መልስ ይጠፋኛል። ምን እንደሚባል ለማን የቱ ጋር ደህና እንዳልሆንሁ እንደምነግረው አላቅም። “አለን¡” አልኩት በተሰላቸ ድምፅ፣ መቼ እንዲህ እንደሆነ አላቅም ብቻ አሁን አሁን ችላ ማለት፣ ከጓደኛ ከቤተሰብ መራቅን እንዲሁ ግዴለሽ መሆንን አብዝቻለሁ። 

“ደህና ነህ ግን አይደል?” አለኝ። ለሦስተኛ ጊዜ ይመስለኛል ሲጠይቀኝ። ከፒያሳ ወደታች በቸርችል ጎደና ወክ እናደርጋለን። ወደኋላ ቆም ብሎ የግራ እጄን ያዝ አድርጎ ” የምሬን እኮ ነው ሄና!” አለኝ። አይኑን ማየት ከበደኝ ፣ እንዲጠይቁኝ ስፈልገው የነበረ ጥያቄ እኮ ነው ግን መልሱ ጠፋኝ። እንዲሁ ሳልናገር ህመሜን እንዲያውቁልኝ እሻለሁ። ከምን እንደሚጀመር ግራ ይገባኛል ብቻ እንባ ቀደመኝ። ደነገጠ! እጄን እንደህፃን ልጅ ይዞ ከመንገድ ማዶ ባለው ካፌ ገባን። ረጅም ዝምታችንን አንዲት ፍልቅልቅ አስተናጋጅ “ምን ልታዘዝ?” ብላ ሰበረችው። “ውሃ ይሻላል። አይደል ሄና? ” ሲለኝ በአዎንታ አንገቴን ነቀነቅሁለት። 

“ምን አዲስ ነገር ተፈጠረ?” አለኝ አይኑን አይኔ ጋ ጥሎ… አቀረቀርኩ።

“ምንም” 

“ምንም (ድምፄን አስመስሎ ደገመው) ይህን ያክል ሩቅ ነን እንዴ ሄና?” አለኝ አይኑን ሳይነቅል። እውነቱን ነው በግቢ ውስጥ ሁሉንም ነገር ሳንደባበቅ ማውራት ምንችለው እኔ እና ቢኒ ነን። 

“እንደሱ ሳይሆን ቢኒዬ ምንም ብነግርህ የሚገባህ አይመስለኝም።”

“እኮ ንገረኝ እና አልገባኝም ልበልህ” አለኝ። ቢኒ ማለት የነፍስያ የሆነ ጓደኛ ነው። የሆነ ፍቅርን በተግባር የሚኖር፣ ቻይነትን የተቸረ በተለይ እኔን የቻለ ምርጥ ጓደኛ ነው። ታዲያ ቢኒን አይሆንም ማለት ይከብዳል።ግን ደሞ ምን ተብሎ ይጀመራል? 

የቱን ማስቀደም ይሻላል? ልጅነቴ ጋ ልጀምር? መሮጥ የሚወደው  እና ከህልሙ ያልተፋታውን ሄኖክ..ከእሱ ልጀምር? ወይስ የአለም ሁሉ ህመም ጀርባው ላይ እንደተሸከመ የጎበጠውን የዛሬውን እኔ? የዕለት ከዕለት ጠቦቼን? ከእኔ እውነተኛው ማንነቴ እና የተሰሩ ፣የቆዩ እና የተካቡ የማህበረሰብ እውነቶች ጋር ያለውን ጠብ ልንገረው?

“ወደ ግቢ እንመለስ። እዛው ብናወራው ይሻላል” አልኩት። ከእግር ወክ ወደታክሲ ገብተን ስድስት ኪሎ ስንደርስ ግቢው ጭልምልም ብሏል። ብዙም ስው የማይበዛበት ቦታ መርጠን ቁጭ አልን።

ልጅነቴ ጥሩ ነበር። እናቴ ትምህርት ቤት የነበረው ቡሊ፣ ስድብ እና የስሞች ጋጋታ ባትከላከልልኝም ቤት ግን ነፃነቴን አውጃልኝ ነበር። ሴታሴት ነህ ይሉኛል። እኮ እላለሁ። አልተሳሳቱም እኮ ችግሩ ሴትነትን እንደስድብ ስለቆጠሩት ሊሰድቡኝ መሞከራቸው ነው። የመጀመሪያ የትምህርት ቤት ዓመታቶቼ በጣም አስደሳች ነበሩ። መሮጥ የማይሰለቸኝ፣ ተጨዋች እና ሳቂታ ነበርሁ። ቤት ደሞ የበለጠ የነፃነት አምባዬ ነበረ። ከትምህርት ቤት እንደመጣሁ ዩኒፎርሜን አሽቀንጥሬ የእናቴን ቀሚሶች አማርጥ እና የሰፈር እኩዮቼን ሰብስቤ “ቤት ቤት እንጫወት” እላቸዋለሁ። ታዲያ እኔ የእናቴን ቀሚስ ለብሼ ለእዛ ሁሉ የሰፈሬ ኩታራ እናት ነበርሁ። የማስታውሰው ታደለ የሚባል ጓደኛዬ ግን ሁሌ ባሌ መሆን ነበር የሚወደው። ልጅ አይደለሁም ባል ነኝ ብሎ ይጣላኝ ሁሉ ነበር። በእነዚህ ጊዜያት እንደወንድ ጓደኞቼ ኳስ አልተጫወትኩም፣ ፈረስ አልጋለብኩም ወይም ብይ እና ቆርኪ ጨዋታወቼ አልነበሩም። ይልቁንም እኔ ከሶስና ከሜሮን እና ከሌሎች ሴት ጓደኞቼ ጋር ያልተጫወትሁት ጨዋታ የለም። 

ነገር ግን እነዚህ ጊዜያት እንደወራጅ ውሃ ተሎ ወርደው አለቁ። በተለይ ሰባተኛ ክፍል ስገባ የእናቴም ቤት ትምህርት ቤቴም ተመሳሳይ ሆኑ። እናቴ ነፃነቴን መንፈግ አትፈልግም ግን ትፈራልኝ ነበር። “ሄኖኬ ወጣ በልና እስኪ ከወንዶች ጋ ተጫወት” ትለኛለች። አሁን ላይ ሆኘ ሳስበው እናቴ ለእኔ ከማሰብ እንጂ እኔነቴን ጠልታው አልነበረም። ግን አልወጣም ነበረ። ያኔ ቤት ውስጥ ከእናቴ ጋር በመሆን በደንብ ስራ አግዛት ነበር። ዛሬ ላይ ልብስ ማጠብ፣ ቤት ማፅዳት ፣ ምግብ ማብሰል (እጅ የሚያስቆረጥም ያውም) የመሰሉ ሙያዎችን በእነዛ ጊዜያት የለመድኳቸው ናቸው።  ትምህርት ቤት ሰባተኛ ክፍል ስደርስ ዝምተኛው ልጅ ሆንሁ። ብዙ ጓደኛ የሌለው: ብዙ የማይስቅ: ግራ የገባው: የሆነ ተፈጥሮው እንደተሳሳተ የሚያስብ ልጅ ሆንሁ። የማስታውሰው የያዙኝን የአይን ፍቅሮች ነው። በተለይ ለአፓረንትሺፕ ከመጣ አንድ የባዮሎጂ መምህር ጋር ስምንተኛ ክፍል ላይ የያዘኝ ፍቅር አሁንም ሳስታውሰው ይገርመኛል።

እውነት ለመናገር ከዘጠነኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል የነበረኝ ህይውት የመደበቅ ነበር። በእዚህ ጊዜ የምደበቀው ከሰው ብቻ አልነበረም ከራሴም ጭምር ነበር። ውስጤ ሁለት ማንነቶችን አርግዞ አንዱን ለማስጨንገፍ እና ለመግደል የሚታገልበት ጊዜ ነበረ። እነዛ አመታቶች ያልተኖሩ ነበሩ እንዳልል ዛሬ ላይ የጠቀሙኝ ነገሮችን የሸመትሁት ከእነዛ ጊዜያት ነው። በተለይ በትምህርት ያለኝን ጉብዝና እና ህመምን እያስታመሙ መርሳትን የለመድሁት ከዛ ነው። የተደበቅሁት ትምህርቴ ላይ እና ሐይማኖት ውስጥ ነበር። ራሴን እንደክርስቶስ ጃንደረባ የምቆጥር ከቤተክርስቲያን ቅጥር የማልጠፋ፣ አትሮንስ ላይ ወጥቼ ወንጌል የሰበኩ ከበሮ ተሸክሜ እንደዳዊት አምላኬን ያመሰገንሁ ነበርሁ። በሐይማኖት በነበረኝ ሂደት ሁለት ነገር የተጠቀምሁ ይመስለኛል። አንዱ ተቀባይነት ማግኘት ነው። ከትልልቅ የሰፈሬ ሰዎች እስከ ትናንሽ ህፃናት ድረስ በሰንበት ትምህርት ቤት በነበረኝ አገልግሎት በክብር ሰላም የሚሉኝ እንጂ ሴታሴት የሚሉኝ አልነበሩም። ሁለተኛው ተስፋ ነው። የሚገድል ተስፋ፣ እንደማይሆን እያወቅህ የምትሞክረው እድል እና የምትጠብቀው ተስፋ አለ አይደል? ብቻ ማንነቴን ወንድ ሆኘ ወንድ መውደዴን እንደህመም ነበር የማየው እና የሆነ ቀን ፈውስ እንደሚሆንልኝ በተስፋ ጠብቅ ነበር።

ሌላኛው መደበቂያዬ ዛሬም ቢሆን ትምህርቴ ነው። አየህ በደቦ መገፋት እና መገለል ሲደርስብህ ሽንፈትህን የምትወጣበት ነገር ትፈልጋለህ። ማህበረሰብ ባወጣው የማንነት መለኪያ ጥሎኝ ያሸነፍኩት በትምህርት ነው። ለዛም ነው ዛሬም ኬኔዲ ላይበራሪን ከዶርሜ በላይ የማዞትረው። 

ግን ምን ያክል ማንነቴን ለመካድና ለመርሳት ብሞክር ፣የቱንም ያክል ብሸሸው ወንድ ሆኘ ለወንድ ልጅ ያለኝ ፆታዊ መስህብ ማንነቴ ነው። አሁን አሁን ሁሉ ነገር ይደክመኛል። ወጥቶ መግባት፣ ከአልጋ መነሳት ብቻ ሁሉ ነገር ሰለቸኝ። አየህ ቢኒ ለምን እንደምነግርህ አላቅም ወይ እንደምታዳምጠኝ ስለአወቅሁ ሊሆን ይችላል። አየህ ለእኔ ማንነቴ የሆነ ወሲባዊ ጨዋታ ብቻ አይደለም ለእኔ ማንነቴ ፍቅር ነው። የሆነ አምስት ደቂቃ የማይቆይ እርካታ አይደለም እንደማንኛውም ሰው ፍቅርን እፈልጋለሁ። የእኔ የምለው፣ ደከመኝ ስለው እኔን የሚለኝ፣ የሚያዳምጠኝ፣ ደስታዬን የማካፍለው ከእንባዎቹ ከድካሞቹ መካፈል የምፈልገው፣ትከሻው ውስጥ ተደብቄ አብሬው ድካሜን የማልፍበት የሚወደኝ የማፈቅረው ሰው እሻለሁ። እና ራሴን በመሆን የነገ ህልሜን በመኖር እና በማያቸው ስድቦች መገፋቶች መካከል ነፍሴ ትጨነቃለች…..እንኳን ወደፊት መሄድ ያለሁበት ቦታ ላይ መቆም የሚከብደኝ ደካማ ሆንሁ……

..የሆነ ሰመመን ነው የመሰለኝ ብቻ ቢኒ እቅፍ ውስጥ ነኝ። ትከሻው በእንባዬ ርሷል። መቼ ትክሻው ጋር እንደደረስኩም አላስታውስም። የራሴው የልቅሶ ሳግ ብቻ ይሰማኛል። 

ትንሽ ቆይተን መረጋጋት ጀመርኩ። የሆነ ነገር ግን ከውስጤ ቅልል ሲለኝ ታወቀኝ።

 “you fine?” አለኝ።

 “yeah, sorry” አልኩት ያስጨነቁት ስለመሰለኝ

“ለምኑ? ወረኛ” አለኝ ሁሌ እንደሚለኝ…..”ሄኒ ምን ማለት እንዳለብኝ አላውቅም። ግን ዛሬ የተዋወቁት ሄኖክ እና የዛሬ ሶስት ዓመት ያለው ሄኖክ ለእኔ አንድ ናቸው። ትናንት የምወድህ ጓደኛዬ ነህ። ብቻ ሄና ህመምህ ምን ያክል ሊሆን እንደሚችል መገመት አልችልም። የመጣህበት መንገድ እንዴት አድካሚ እንደሆነ ማሰቡ ራሱ ያደክማል። ብቻ ግን ጠንካራ ሁን እና በእናትህ ተስፋ አትቁረጥ። ነገ በህይወት ውስጥ ምን happen ሊያደርግ እንደሚችል አናውቅም። just ህልምህን አትልቀቀው የሆነ ቀን የሆነ ስዓት የህይወታችን አቅጣጫ ይቀየራል for sure….ታቃለህ ማውራት አልችልም….can i get a hug?” አለኝ እና ቆመ። ረጅም ስዓት አቅፎ እንደህፃን ልጅ አባበለኝ።….ያስጨነኩት ሲመስለኝ ከእቅፉ ወጥቼ ስዓቴን አየሁ። አራት ስዓት ሆኗል። ወደዶርም ማዝገም ጀመርን። ዶርም ስንደርስ ቢኒ “ሄኒ ግን እንዴት ለመንገር ደፈርክ?” ብሎ ጠየቀኝ።

“አላቅም!” ነበር ያልኩት። እንዴት ደፍሬ ማንነቴን ለአንድ ጓደኛዬ እንደነገርኩት አላቅም። ዛሬም ይኸው ድፍረት ይመስለኛል እንድኖር የሚያደርገኝ። 

ያንን ቀን ሳስበው በህይወቴ ከምደሰትባቸው ቀናት ውስጥ ነው። በድካሜ ውስጥም እንኳን ሁሌ የሚደግፈኝ ጓደኛ ያገኘሁበት ቀን ነው። ማንነቴን እንድቀበል ብቻ ሳይሆን ማንነቴ ከህይወት ህልሜ፣ አሳከዋለሁ አደርገዋለሁ ካልኩት ነገዬ እንደማያደናቅፍኝ የተረዳሁበት ቀን ነው። ከምንም በላይ በደቦ አስቦ በደቦ የሚወግር ማህበረሰብ ውስጥ የፍቅር ክንዳቸውን የሚያውሱ ሰዎች እንዳሉበት ያወቅኩበት ቀን ነው።

HenaAb @2016

Share